አፍማማ በኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ላይ ለሚያጋጥሙ ዘጠኝ እርስ በርስ የተሳሰሩ ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት ተመሠረተ።
01
የአካባቢ መራቆት እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት
በኢትዮጵያ እንደአብዛኛዉ የአለማችን ክፍል የአካባቢ መራቆት እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ፈተናዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ ይገኛሉ። ይህም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነ-ምህዳራዊ እና የህዝብ ጤና ቀውሶችን አስከትሏል። እነዚህ ተግዳሮቶች በዋነኛነት የሚከሰቱት ማህበረሰብን መሰረት ያደረጉ እና ስነ-ምህዳራዊ-ተኮር የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረትን የመቋቋም ስልቶች ተነድፈዉ ባለመተግበራቸዉ ነዉ፡፡
02
ፍትሃዊ የኢነርጂ ሽግግር አስፈላጊነት
ሃይል በተለይም ታዳሽ ሃይል ለዘላቂ ልማት እና ለኑሮ ደህንነት ወሳኝ ነው። ይሁን እንጂ በርካታ ጥናቶች እንደሚሳዩት ታዳሽ ኃይልን በተለይም በገጠር እና የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ሰፊ ዉስንነቶች አሉ፡፡ ይህ ኢፍትሃዊነት የኢነርጂ ድህነትን ያስፋፋል፣ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከብሄራዊ የኃይል ሽግግር ጥቅሞች እንዲገለሉ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ጥናትን መሰረት ያደረጉ ስራዎች መሰራት አለባቸዉ፡፡
03
ኃላፊነት የሚሰማው የመሬት እና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ፍላጎት
በኢትዮጵያ መሬት እና ከመሬት ጋር የተያያዙ የተፈጥሮ ሀብቶች እጅግ ወሳኝ እና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ፣አካባቢያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸዉ፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ የመሬት መብቶችን ዕዉቅና በመስጠት፣በማስተዳደር እና በማስከበር ላይ ወሳኝ ክፍተት ይስተዋላሉ፡፡ ይህም የይዞታ ደህንነትን የሚጎዳ፣ መሬትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን የሚያባብስ እና የህብረተሰቡን የተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ወደ ጎን ገሸሽ የሚያደርግ ነዉ፡፡ እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አስቸኳይ ክትትልና ድጋፍ ይጠብቃሉ።
04
የፍትህ ተደራሽነት እና የህግ ማብቃት ጉድለት
ፍትህ የፍትሃዊ የህግ ስርዓቶች እና የህዝብ አስተዳደር መለያ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ለዚህም ነው የፍትህ ተደራሽነት በብዙ አለም አቀፍ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች እውቅና ያገኘው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም የሴቶች፣ አርብቶ አደር እና የገጠር ማህበረሰቦች መብታቸውን ለመጠየቅ የሚያስችል ሃብትና እውቀት የላቸዉም፡፡ በተለይም መደበኛዉ የፍትህ ስርዓት ውስብስብ እና ተደራሽ ባለመሆኑ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የፍትህ ክፍተት እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ በዚህም አፋጣኝ እና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ስራዎች መሰራት አለባቸዉ፡፡
05
የባለብዙ ደረጃ አስተዳደር ዲሞክራሲያዊ ጉድለት
የህዝብ አስተዳዳር በተለይም በአከባቢ ደረጃ ያለው አስተዳደር ልማትን ወደ ፊት ለማራመድ እና ዴሞክራሲያዊ መረጋጋትን ለማስቀጠል ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የአካባቢ አስተዳደር የአካባቢ መንግስታትን፣ ዜጎችን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን፣ የግሉ ሴክተርን እና አንዳንዴም ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ አካላትን ጨምሮ ውስብስብ ተዋንያንን ያካትታል። ነገር ግን፣ በኢትዮጵያ፣ አሳታፊ አስተዳደርን ከማረጋገጥ አንፃር ሰፊ እና መዋቅራዊ ክፍተቶች እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በዚህም ቁልፍ ባለድርሻ አካላት በተለይም የአካባቢ ማህበረሰቦች በኑሮአቸው እና በልማት ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ውሳኔ ሰጪ ሂደቶች ላይ በተደጋጋሚ ይገለላሉ። በተጨማሪም፣ ማዕከላዊ የመሪነትና የማስተባበር ሚና የሚይዙት የአካባቢ መስተዳድሮች ራሳቸውን ችለው የተቋቋሙና በቂ አቅም ያላቸው አይደሉም። ይህ ባለድርሻ አካላትን ያገለለ አስተዳዳር እና የአካባቢ ምንግስታትን በሚፈለገዉ መልኩ አቅማቸዉን ማጎልበት አለመቻል የአስተዳደርን ጥራት፣ ህጋዊነት እና ዘላቂነት ያዳክማል፡፡ ይህም አስቸኳይ እና የታቀዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን ይፈልጋል።
06
ለታችኛው ፖሊሲ እና የህግ ማሻሻያ አስፈላጊነት
ዘርፈ-ብዙ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የአካባቢ አስተዳደር ከማጠናከር ጎን ለጎን የፖሊሲ እና የህግ ማሻሻያዎችን ከታች ጀምሮ እስከ ላይ በሚደርሱ ሰንሰለቶች እንዲያልፉ ማድረግ ተቀባይነት እያኘ የመጣ አሰራር ነዉ፡፡ ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ሁሉን አቀፍ ፖሊሲ ማውጣት ላይ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ የህዝብ ድምጽ በፖሊሲ እና ህግ ማዉጣት ሂደቶች ውስጥ እምብዛም አይካተትም። ይህ ክፍተት ብዙውን ጊዜ ከአካባቢው እውነታዎች ጋር የተንሰላሰሉ ፖሊሲዎችና ህጎች እንዳይወጡ ወይም ማሻሻያዎች እንዳይደረጉ ያደርጋል፡፡ ይህ ክፍተት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ንቁ ተሳትፎ እና ስልታዊ ድጋፍ ይጠይቃል።
07
አከባቢያዊ የሰላም ግንባታ እና ማህበራዊ ትስስር አስፈላጊነት
የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መራቆት እንደ ውሃ እና ለም መሬት ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶችን በማሳሳት በማህበረሰቦች መካከል ለግጭት መንስኤ እየሆነ በመምጣቱ፣ ማዕከሉ እነዚህን የጋራ ሃብቶች በፍትሐዊነት ማስተዳደር እና አብሮ የመንከባከብ ባህልን በማሳደግ፣ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን እንደ ማህበራዊ ትስስር እና መተማመን መፍጠሪያ መድረክ በመጠቀም ማህበረሰቡ ለጋራ ጥቅሙ በአንድነት እንዲቆምና ዘላቂ ሰላም እንዲገነባ ያደርጋል።
08
በልማት ሂደት የሰብዓዊ መብት ጥሰት
በትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ምክንያት የሚከሰቱ ያለፍላጎት መፈናቀሎች፣ የተገቢ ካሳ እጥረት እና በፋብሪካዎች መርዛማ ቆሻሻ ሳቢያ የሚፈጠረው የአካባቢ ብክለት የማህበረሰቡን በጤናማ አካባቢ የመኖርና ንጹሕ ውሃ የማግኘት ሰብዓዊ መብቶች የሚጥሱ በመሆናቸው፣ ማዕከሉ ማንኛውም የልማት ሥራ የአካባቢውን ተወላጆች መብት ባከበረ፣ ንቁ ተሳትፎን ባረጋገጠ እና ‘አረንጓዴ ፍትሕን’ በተከተለ መልኩ እንዲከናወን በሕግና በፖሊሲ ደረጃ ይሞግታል።
09
የዘርፍ-አቀፍ ትብብር እና አጋርነት አስፈላጊነት
ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም ክፍተቶች የሁሉንም ባለድርሻ አካላት በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ እርምጃ እና አጋርነት ይፈልጋሉ። እንደ አለመታደል ሆኖ፣ ሰፊ የቅንጅትና አጋርነት ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡ ይህም ባለድርሻ አካላት ለተወሳሰቡ የአካባቢ እና የአስተዳደር ተግዳሮቶች የተቀናጀ የመፍትሄ አቅጣጫ እንዳይዘጋጅ እንቅፋት ሆኖ ቆይተዋል። በዚህም ትብብርን እና አጋርነትን እንደ አንድ የትኩረት ነጥብ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
